ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ወቅታዊ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል። የመግለጫው ሙሉ መልእክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ጠላት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን የማፍረስ ህልሙን እና የአማራን ህዝብ በጉስቁልና አዙሪት ዉስጥ ለማቆየት ድፍን አንድ አመት በሚባል ደረጃ በአለች በሌለች ደካማ አቅሙ ማድረግ የሚችለውን ሰይጣናዊ ድርጊት ሲፈፅም ተመልከተነዋል።

በተለይም ጠላት አልቻለም እንጂ ፍርስራሿ ላይ መቆም ከሚፈልጋቸው ቦታዎች ግንባር ቀደሟ የባህር ዳር ከተማ ናት። ሰላም ወዳዱ፣ ሰርቶአዳሪው የባሕር ዳር ነዋሪ፣ የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች፣ ለክልሉ እና ለከተማ አስተዳደሩ ጥምር የፀጥታ ኃይል ጥረት እና ጥምረት ከተማችን ባህር ዳር ሰላምና ፀጥታዋ በአንፃራዊነት ተጠብቆ ህዝቡን የሚጠቅሙ ዘርፈ ብዙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ሲከናወኑ ከርሟል።

በዚህ ዘወትር የሚበሳጨው እና ቅቱ እውን ባለመሆኑ እረፍት ያጣው ጠላት ከነሀሴ 7/2016 ዓ.ም ም ጀምሮ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲቆም አዋጅ አስነግሮ የነበረ ቢሆንም የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የዚህ እኩይ ተግባር ተባባሪ ሳይሆን በመቅረቱ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውና ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ሳይስተጓጎሉ ቀጥለዋል። በዚህ የተበሳጨው ጠላት በከተማዋ የተወሰኑ ጥቂት ቦታዎች ጊዜ ሰጭ ፈንጂ በማፈንዳት ከተማውን የማሽበር ስራ ፈጽሟል። ይህም ተደርጎ የጠላት ዕቅድ አልተሳካም።

በእነዚህ ውድቀቶቹ ተስፋ ያስቆረጠው ጠላት ዛሬ ነሀሴ 10 / 2016 ዓ.ም ከቀኑ 7:00 ጀምሮ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ባስተላለፈው ዛቻና ማስፈራሪያ የከተማው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባጃጅና ታክሲ እንዲያቆሙ ፣ በተወሰነ የከተማው ክፍል የንግድ ድርጅቶችና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በስጋት አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጓል።

በጉዳዩ ላይ ጥምር የፀጥታ ሀይሉና የከተማው አመራር ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት አድርጓል።

ክስተቱ የተፈጠረውም በስጋትና በመደናገር መሆኑን መግባባት ላይ ተደርሷል። በመንግስት በኩል በቂ ዝግጅት ያለ መሆኑንና በከተማችን ምንም የፀጥታ ሰጋት ሊሆን የሚችል ነገር እንደሌለ፣ ለከተማዋና ለነዋሪዎች አስተማማኝ ጥበቃ እየተደረገ እንደሆነ፣ ህግ የማስከበር ዝግጁነቱን በውይይቱ አረጋግጧል።

በነገው ዕለትም ከተማዋ ወደ መደበኛ ሁኔታዋ እንድትመለስ መግባባት ላይ ተደርሷል።

ስለሆነም በነገው ዕለት የትራንስፖርት ማህበራት እና ድርጅቶች፣ የንግድና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ የመንግስት ተቋማት መደበኛ አገልግሎት መስጠት ይጀመራሉ።

በመሆኑም መላው የከተማችን ነዋሪ በማህበራዊ ሚዲያ በሚለቀቅ የሽብር ወሬና አሳሳች ዜና ሳይደናገር መደበኛ እንቅስቃሴውን ያለምንም ስጋት እንዲቀጥል ከተማ አስተዳደሩ ያሳስባል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር