ለቸኮለ ማለዳ! ቅዳሜ ነሐሴ 11/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

ለቸኮለ ማለዳ! ቅዳሜ ነሐሴ 11/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1 የአማራ ክልል መንግሥት ጸጥታ ቢሮ፣ በዛሬው ዕለት ባሕርዳር ከተማ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እንድትመለስ ከነጋዴዎችና የትራንስፖርት ማኅበራት ጋር ከስምምነት ላይ እንደተደረሰ አስታውቋል። ቢሮው፣ የትራንስፖርት ማኅበራትና ድርጅቶች፣ የንግድና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንዲሁም የመንግሥት ተቋማት ዛሬ መደበኛ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ገልጧል። ትናንት የፋኖ ታጣቂዎች አስተላልፈውታል በተባለው የጥቃት ዛቻ ሳቢያ፣ በከተማዋ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችና የንግድ ድርጅቶችና አገልግሎቶች ተቋርጠው ነበር።

2፤ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር፣ የስንዴ ዱቄትና ሩዝን ጨምሮ በምግብና የግንባታ ዕቃዎች ላይ መጠነኛ የዋጋ ቅናሽ መታየቱን አስታውቋል፡፡ በተያያዘ፣ ትናንት ብቻ ያላግባብ ዋጋ የጨመሩ 479 የንግድ ድርጅቶች የታሸጉና የ5 የንግድ ድርጅቶች ፍቃድ የታገደ ሲኾን፣ ምርት የደበቁ የንግድ ሦስት ተቋማት ደሞ ንደታሽጉና የስድስቱ ንግድ ፍቃድ እንደታገደ ሚንስቴሩ ገልጧል። በግንባታ ዕቃዎች ላይ ሕገወጥ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 23 የሲሚንቶ፣ 12 የብረት፣ 19 የቆርቆሮና 5 የሚስማር መሸጫ ንግድ ድርጅቶችም ታሽገዋል ተብሏል።

3፤ የአማራና ትግራይ ክልሎች ለሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች መፍትሄ ለማፈላለግ የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ የእስካኹኑ እንቅስቃሴው ስኬታማ መኾኑን መግለጡን፣ የወሎ አማራ የማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ተጨባጭ እውነታውን የካደና በራያ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመውን ግፍ የዘነጋ ነው በማለት እንደተቃወመው ዶይቸቨለ ዘግቧል። የማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴው፣ ከአለማጣ ከተማ የተናቀሉ ከ70 ሺሕ በላይ የአማራ ብሄር ተወላጆች እስካሁን ወደቀያቸው መመለስ እንዳልቻሉ መናገሩን ዘገባው አመልክቷል። በራያ አላማጣ ካሉት ከ56 ቀበሌዎች 44ቱ በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ተናግሯል ተብሏል። ዐቢይ ኮሚቴው ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ በራያ አላማጣ ተፈናቃዮችን የመመለሱ ጥረት ስኬታማ ኾኗል በማለት ተናግሮ ነበር።

4፤ አንድ የብሪታንያ ንግድ መርከብ በምጽዋ አቅራቢያ በዓለማቀፍ ባሕር ላይ ሲያልፍ የታጠቁ ሰዎችን የጫነች የኤርትራ ባሕር ኃይል ጀልባ በቅርበት እንደተጠጋችው የተለያዩ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። አንዳንድ ያልተረጋገጡ መረጃዎች ደሞ፣ በመርከቡ ላይ ከጀልባዋ መሳሪያ እንደተተኮሰበት ጠቅሰዋል። ቀይ ባሕር ላይ የየመን ሁቲዎች በንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ የቆዩም ቢሆንም፣ የኤርትራ የባሕር ኃይል ጀልባ በዓለማቀፍ ባሕር ላይ ወደሚንቀሳቀስ የሌላ አገር የንግድ መርከብ ስትጠጋ ግን የሰሞኑ የመጀመሪያ ክስተት እንደኾነ ተገልጧል። [ዋዜማ]

https://youtube.com/@wolloaddis11?si=kWY7W8qt5igRY-a8