” ሁሉንም የፓለቲካ ሃይሎች ያቀፈ መንግስት በአስቸኳይ መመስረት ያስፈጋል ” – ሦስት የፓለቲካ ፓርቲዎች
በትግራይ የሚንቀሳቀሱት ባይቶና፣ ሳወት፣ ናፅነት የፓለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ ፤ ” ሳምንቱን በስርዓቱ ባለቤቶች መካከል በመካሄድ ያለው ህገ-ወጥ እንቃስቃሴና ፍጥጫ ተው መባል ይገባዋል ” ብለዋል።
በህወሓት አመራሮች የተፈጠረው ፍጥጫ ተከትሎ በህዝቡ የሚታየው መረበሽ ያወገዙት ሦስቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ” ህግ እየጣሱ በህዝብ ካባ ስም ለመደበቅ የሚደረገው መሯሯጥ እናወግዛለን ” ሲሉ ገልጸዋል።
” ለቡድናዊ ጥቅም ሲባል በህዝብ ቁማር መጫወት መቆም አለበት ” ያሉት ፓርቲዎቹ ” ደርጅታዊ ይሁን ቡድናዊ ጉዳይ ከህዝብ ህልውና ማጣበቅ እንፀየፈዋለን እንዲቆምም እናሳስባለን ” ብለዋል።
” የህዝብ ሰላም፣ ህልውናና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ህገ-ወጥ ፓለቲካዊ ተግባር ሲታ የሚመለከተው የፀጥታ አካልና ህዝብ ያለማዳላት በአስቸኳይ የማስቆም ሃላፍነቱን መወጣት አለበት ” ሲሉም ገልጸዋል።
” የተፈጠረው ፓለቲካዊ አለመረጋጋት ዋነኛ መፍትሄው ሁሉም የፓለቲካ ሃይሎች በእኩልነት የሚሳተፉበት መንግስት በአስቸኳይ መመስረት ነው ” የሚል የመፍትሄ ሀሳብ አቅርበዋል። ፓርቲዎቹ ፤ ሁሉም የፓለቲካ ሃይሎች በእኩልነት የሚሳተፉበት መንግስት በአስቸኳይ የመመስረት ጥሪ በተደጋጋሚ ማቅረባቸውና ግን ሰሚ አለማግኘታቸው አመልክተዋል።

